ባህላዊ የእስልምና ትምህርት መገለጫዎች፣ለውጦችና ወቅታዊ ተጨባጮች በወሎ ቃሉና ቦረና አካባቢዎች
DOI:
https://doi.org/10.20372/ajcik.2022.1.1.693Abstract
ጥናቱ የተካሄደው ‹‹ባህላዊ የእስልምና ትምህርት መገለጫዎች፣ለውጦችና ወቅታዊ ተጨባጮች በወሎ ቃሉና ቦረና አካባቢዎች›› በሚል ርዕስ ሲሆን የባህላዊ ትምህርቱን መገለጫዎች በማብራራት ለውጦችንና ወቅታዊ ተጨባጩን መተንተን የጥናቱ ዋና አላማ ነው፡፡ ጥናቱ አይነታዊ ምርምርን ተከትሎ ተካሂዷል፡፡ በመሆኑም ቃለ መጠይቅ ምልከታና የተተኳሪ ቡድን ውይይትን በመረጃ መሰብሰቢያነት፣ ገላጭ የመረጃ መተንተኛ ዘዴን ደግሞ በመረጃ መተንተኛነት ተጠቅሟል፡፡ የጥናቱ ውጤት እንደሚያመለክተው ባህላዊው የእስልምና ትምህርት እንደማስተማሪያ ዘዴነት ሸሪካ፣ ሙጠላ፣ መዋጣት፣ መከረር(መሀፈዝ)፣ መሰማትና ውርድ የተባሉ ልማዶችን ይጠቀማል፡፡ ተማሪዎች ደረሳ የሚባሉ ሲሆን በአዳሪነትና በተመላላሽነት ትምህርታቸውን ይከታተላሉ፡፡ ትምህርቱ ቁርአንና ኪታብ ተብሎ የሚከፈል ሲሆን በቁርአን ጁዝ የሚባል ክፍልፋይ አለው፡፡ በዚህም የተማሪው የትምህርት ደረጃ ይገለጻል፡፡ በኪታብ ደግሞ በሚማረው ኪታብ ስም ደረጃው ይታወቃል፡፡ ይህ የትምህርት ደረጃ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ውስጥ ቋሚ የሆነ እውቀትን መነሻ ያደረገ መዋቅር እንድፈጠር አስችሏል፡፡ በመሆኑም ባህላዊው የእስልምና ትምህርት የህብረተሰብን ታህታይ መዋቅር ለማስጠበቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ጥናቱ አረጋግጧል፡፡ ባህላዊው የእስልምና ትምህርት ገጠርን ማዕከል ያደረገ፣ ጠንካራ ተቋማዊ መሰረት ያለው፣ ሀገር በቀል ስርዓተ ትምህርትን በወጥነት የሚጠቀም፣ በአብዛኛው ለፊቅህና ለቋንቋ ትምህርቶች ትኩረት የሚሰጥ መሆኑ መገለጫዎቹ ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር አሁን ባለው ተጨባጭ በባህላዊ ትምህርቱ ላይ ለውጦች እንደተከሰቱም በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡ በመሆኑም ባህላዊ ትምህርቱ ከገጠር ወደ ከተማ በመዘዋወር ላይ እንደሆነ ፣ከጠንካራ ተቋማዊነት ይልቅ ትስስር በሌለው የተቋሞች አደረጃጀት አልፎ አልፎም በግለሰባዊነት ደረጃ በመሰጠት ላይ እንደሚገኝ፣ ወጥ የሆነ ስርዓተ ትምህርትን እየተከተለ እንዳልሆነ፣ ከይዘት አንጻር ደግሞ ከፊቅህ ለሀድስና ለተፍሲር ትምህርቶች ትኩረት ሰጥቶ እንደሚያስተምር ጥናቱ አረጋግጧል፡፡ እነዚህ ለውጦች ደግሞ በሙስሊሙ ማህበረተሰብ መካከል ተመሳሳይ ሐይማኖታዊ ግንዛቤ እንዳይኖር፣ ሰፊው የገጠሩ ሕብረተሰብ ትምህርቱንና ጭብጡን አዲስ ብሎ በጥርጣሬ እንዲያየው፣ እንዲሁም በህብረተሰቡ መካከል የነበረው እውቀትን መሰረት ያደረገ መዋቅር እንዲፋለስና ግለሰቦች ሃይማኖታዊ ደረጃቸው እንዳይታወቅ ብሎም የማእረግ ስሞች በተገቢው ሁኔታ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ አድርጓል፡፡