በራስ መር የመማር ብልሃት መጻፍን መማር የመጻፍ ችሎታን ለማጎልበት ያለው ሚናና የተነሳሽነት ደንጋጊነት ትንተና -በ11ኛ ክፍል ተተኳሪነት
DOI:
https://doi.org/10.20372/ajcik.2022.1.1.692Abstract
የጥናቱ ዋና ዓላማ በራስ መር የመማር ብልሃት መጻፍን መማር የመጻፍ ችሎታን ለማጎልበት ያለውን ሚና መመርመር ነው፡፡ ጥናቱ መጠናዊ ምርምር እና ፍትነት መሰል የጥናት ንድፍን ተከትሎ ተሰርቷል፡፡ በጥናቱ ሂደትም ሁለት ቡድኖች (የሙከራ ቡድንና የማመሳከሪያ ቡድን) ያሉ ሲሆን የሙከራ ቡድኑ በራስ መር የመማር ብልሃት፣ የማመሳከሪያ ቡድኑ ደግሞ ያለብልሃቱ(የክፍል ደረጃው የመጻፍ ክሂል ትምህርት) በቀረበበት መንገድ የመጻፍ ክሂል ትምህርትን ለ6 ሳምንታት ለ12 ክፍለ ጊዜያት እንዲማሩ ተደርጓል፡፡ በጥናቱም በደሴ ከተማ በሆጤ አጠቃላይ ከፍተኛ ትምህርት መሰናዶና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደረጃ ትምህርት ቤት በ2012 ዓ.ም በመማር ላይ የሚገኙ 28 የ11ኛ ክፍል መማሪያ ክፍሎች መካከል በተራ ዕጣ ናሙና ዘዴ የተመረጡ ሁለት የመማሪያ ክፍሎች ምድብ (16) የማመሳከሪያ ቡድን 42፣ ምድብ (19) የሙከራ ቡድን 54 በድምሩ 96 ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ ለእነዚህ ተሳታፊዎች በቅድመ ትምህርትና በድህረ ትምህርት የመጻፍ ችሎታ ፈተናና የመጻፍ ተነሳሽነት መጠይቆች በመስጠት መረጃዎችን ለመሰብሰብ ተችሏል፡፡ የተገኙ መረጃዎችም በባዕድ ናሙና ቲ ቴስት፣ በማን ዊትኒ ዩ ኢ ፓራሜትራዊ ትንተና፣ የደንጋጊነት ትንተና ሞዴል 4ን መሰረት በማድረግ ተተንትነዋል፡፡ የጥናቱ ግኝትም በተለመደው የመጻፍ ትምህርት አቀራረብ ከተማሩ ተማሪዎች ይልቅ በራስ መር የመማር ብልሃት መጻፍን የተማሩ ተማሪዎች በመጻፍ ችሎታቸው እና በመጻፍ ተነሳሽነታቸው ላይ የበለጠ መሻሻል የታየ መሆኑን መገንዘብ ተችሏል፡፡ በአንጻሩ የመጻፍ ተነሳሽነት የደንጋጊነት ሚናው የጎላ አለመሆኑን መረጃዎች አመላክተዋል፡፡ ከጥናቱ ግኝት በመነሳትም የመፍትሄ ሃሳቦች ተጠቁመዋል፡፡