የሀሳብ ማደራጃ ቢጋሮችን መማር በአማርኛ ቋንቋ የመጻፍ ክሂል ችሎታንና የመጻፍ ተነሳሽነትን ለማጎልበት ያለው ሚና፤ በ9ኛ ክፍል ተማሪዎች ተተኳሪነት ያለው ሚና፤ በ9ኛ ክፍል ተማሪዎች ተተኳሪነት
DOI:
https://doi.org/10.20372/ajcik.2022.1.1.691Abstract
የጥናቱ ዋና ዓላማ በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት በሀሳብ ማደራጃ ቢጋሮች ታግዞ መጻፍን መማር የተማሪዎችን የመጻፍ ችሎታ እና የመጻፍ ተነሳሽነት ለማሻሻል የሚኖረውን ሚና መፈተሽ ነው፡፡ ዓላማውን ለማሳካትም መጠናዊ ምርምር ብሎም ፍትነትመሰል የጥናት ንድፍ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ በመሆኑም በሀሳብ ማደራጃ ቢጋሮች መጻፍን የሚማር ቡድንና ያለሀሳብ ማደራጃ ቢጋሮቹ በተለመደው መንገድ መጻፍን የሚማር ቡድን ተለያይተው የመጻፍ ክሂል ትምህርትን በ8 ሳምንታት ለ17 ክፍለጊዜያት ተምረዋል፡፡ የጥናቱ ተሳታፊዎችም በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኘው በአጣዬ ከተማ የከፍተኛ መሰናዶ ትምህርትና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት በ2010 ዓ.ም በዘጠነኛ ክፍል ተመዝግበው በ17 የመማሪያ ክፍሎች ሲማሩ ከነበሩት ውስጥ በተራ እጣ ንሞና ዘዴ በተመረጡ ሁለት መማሪያ ክፍሎች የተገኙ ማለትም በሙከራ ቡድኑ 46፣ በቁጥጥር ቡድኑ 46 በጥቅሉ 92 ተማሪዎች ናቸው፡፡ ከተሳታፊዎቹም ቅድመትምህርትና ድህረትምህርት የመጻፍ ችሎታ በፈተና፣ ቅድመትምህርትና ድህረትምህርት የመጻፍ ተነሳሽነት በመጠይቅ አማካይነት ተለክተው መረጃዎች ተሰብስበዋል፡፡ መረጃዎቹም በአማካይ ውጤት፣ በመደበኛ ልይይት፣ በባዕድ ናሙና ቲ-ቴስት ተሰልተው ተተንትነዋል፡፡ የጥናቱ ግኝቶች እንዳመላከቱትም ያለሀሳብ ማደራጃ ቢጋሮቹ በተለመደው መንገድ መጻፍን ከተማሩት ተማሪዎች ይልቅ በሀሳብ ማደራጃ ቢጋሮች ታግዘው መጻፍን የተማሩት በመጻፍ ችሎታቸው ጉልህ (t(90)= 4.974፣ P=0.000) መሻሻል ከማሳየታቸው ባለፈ የተጽዕኖ ደረጃው (effect size) ከፍተኛ ሆኖ (eta squared = 0.22) ተገኝቷል፡፡ በተመሳሳይ በመጻፍ ተነሳሽነታቸውም በሀሳብ ማደራጃ ቢጋሮች የተማሩት ተማሪዎች ጉልህ (t(90)= 2.742 ፣ P=0.007) መሻሻል አሳይተዋል፤ መካከለኛ የተጽዕኖ ደረጃ (eta squared = 0.077) አሳይቷል፡፡ ከጥናቱ ግኝቶች በመነሳትም በአማርኛ ቋንቋ በሀሳብ ማደራጃ ቢጋሮች መጻፍን መማር የተማሪዎችን የመጻፍ ችሎታ ያዳብራል፤ ብሎም የመጻፍ ተነሳሽነት ያሻሽላል ወደሚል ድምዳሜ ተደርሷል፡፡ ከግኝቶቹ በመነሳትም ስነትምህርታዊ የመፍትሄ ሀሳቦች ተጠቁመዋል፤ የወደፊት የምርምር አቅጣጫዎችም ተመላክተዋል፡፡